ስለ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለኢትዮጵያውያን! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

የአዲሱ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ቢከሰት የመቆጣጠር ኃይል ያላቸው የበለጸጉት አገሮች መራወጥ የጀመሩት ወዲያዉኑ በቫይረሱ የተለከፉ የመጀመሪያዎች በሽተኞች ቻይና ውስጥ እንደታወቁ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወረርሽኙ ቢከሰት የዝንጀሮና የጦጣ ያህል የመከላከያ ኃይል የሌላቸው አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነፍሰ ገዳይ ገዥዎች እስካሁን ለንቦጫቸውን ጥለው ተእቁባቶቻቸው ጋር እንደተኙ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም ቫይረሱ በነገሰባቸው አገሮች እየበረረ ሕዝብ ሲጨፈጭፉ፣ ሲገርፉ፣ ሲያመክኑና ሲያሰድዱ ለኖሩ ሰው በላዎች ገንዘብ መሰብሰቡን እንደቀጠለ ነው፡፡

እነዚህ አምባ ገነኖች እነሱ እንደ ተራ ሰው የሚኖሩ ዜጎቾ፤ ሚስቶቻቸው ከምስኪን ሴቶች ጋር ውሀ የሚቀዱ፣ ቡና እሚጣጡ፣ ቤተክሲያን ወይም መስጊድ የሚስሙና እቁብ የሚጥሉ፤ ልጆቻቸውም እንደ ድሀ ልጅ ዳስ ውስጥ ተፋፍገው የሚማሩ ቢሆኑ ኖሮ እንደ በለጸጉት አገሮች ቫይረሱን ለመቆጣጠር ሲራወጡ ይታይ ነበር፡፡ ዳሩ ግን እነሱ እንኳን በቫይረሱ ከተበከለ ልብሱ ከተቀደደ ሰው ጋርም አብረው ውለው ስለማያድሩ፣ ሚስቶቻቸውም ቪላ ውስጥ በበርካታ ገረዶች ሲጨጎሉ ስለሚውሉና ልጆቻቸውም በድሃ ገንዘብ ከበለጸጉት አገሮች አለዚያም የበለጸጉት አገሮች በከፈቷቸው ውድ ትምህርት ቤቶች ስለሚማሩና  እንኳን  በቫይረስ በባሩድም ሕዝብ ጨፍጭፈው ስለማይጠየቁ እንደ ተለመደው ተሰው ነፍስ ገንዘብን መርጠው ጥንቃቄ ማድረጉን ችላ እያሉ ነው፡፡

ስለዚህ ሕዝብ እርስ በራሱ እየተማማረና እየተረዳዳ ራሱን፤ ቤተሰቡንና ጎረቤቱን በቫይረሱ ተመለከፍ ለማዳን ጥረት ማድረግ ያሸዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ያለው አብሮ የመብላት፣ አብሮ የመኖር፣ አብሮ የመጸለይ፣ እድርና እቁብ የመጣል፣ የቡና ቲራቲም፣ ደቦና ወንፈል የመሳሰሉት የአኗኗር ዘዴዎች የቫይረሱን  በፍጥነት የመሰራጨት ሂደት ያባብሱታል፡፡

በአገራችን የቫይረሱን ስርጪት ለመከላከል ይረዳ ዘንድ ለሕዝባቸው የሚያስቡና ተጠያቂነት የሚሰማቸው መንግስታት ቫይረሱን ለመቆጣጠር ያደረጉትን ምርምርና እቅድ በመፈተሽ የሚከተለው በአማርኛ ቀርቧል፡፡

  1. ኮሮና ቫይረስ-19 ምንድነው? ኮሮና ቫይረስ የብዙ ቫይረስ ዓይነቶች ጥቅል ቤተሰባዊ ስያሜ ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስ-19 በዚህ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ በዚህ ዓመት የተከሰተ አዲስ ቫይረስ ነው፡፡

 

  1. የቫይረሱ የመጀመርያ ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል? ቫይረሱ በውሻ ቤተሰብ ወይም በድመት ቤተሰብ በሚመደቡ እንደዚሁም በሌሎች እንሰሳዎች አካል ሊኖር ይችላል፡፡

 

  1. ቫይረሱ እዴት ይተላለፋል? ቫይረሱ ከእንሰሳ ወደ ሰው እንደዚሁም በእስተንፋስ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡ ይህም ማለት እርስዎ በቫይረሱ ከተበከለ ሰው ሁለት ዘለግ ያለ እርምጃ ያህል ከተገኙ ቫይረሱ ሊጋባብዎት ይችላል፡፡ እነደዚሁም በቫይረሱ የተበከለውን እጅ ጨብጠው በደንብ በሳሙና ካልታጠቡ ከራስዎ እጅ ቫይረሱ ወደ እስተንፋስዎ ሊገባ ይችላል፡፡

 

  1. የበሽታው ምልክት ቫይረሱ ወደ እስተንፋስ በገባ በስንተኛው ቀን ምልክት ሊያሳይ ይችላል? ይህ በመጠናት ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ተዚህ በፊት የተከሰቱትን ኮሮና ቫይረሶች ጥናት መሰረት በማድረግ ከ2-14 ቀናት ውስጥ ምልክት እነደሚያሳይ ተገምቷል፡፡ አብዛኛው በቫይረሱ የተለከፈ ሰው ግን ምልክት ሳያሳይ የቫረሱ ተሸካዊ ሆኖ ይቆያል፡፡ ቫይረሱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ይኸ ነው፡፡ ተሸካሚው ምልክት ሳያሳይ ቫይረሱን ወደ ሌላ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡

 

  1. ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? ምልክቶቹ ከሌሎች ሳል ተሚያመጡ ቫይረሶች እምብዛም የተለዩ አይደሉም፡፡ ዋና ዋናቾቹ ሳል፣ ትኩሳትና የእስተንፋስ እጥረት ናቸው፡፡

 

  1. በሽታው በምን ይረጋገጣል? በሽታው የጤና ባለሙያው በሽተኛውን ጠይቆ ከሚያገኘው የንክኪ መረጃና የበሽታው ምልክቶች በተጨማሪ በላቦራቶሪ ይረጋገጣል፡፡ ለላቦራቶሪው የሚሆን ናሙና እንደ ሁኔታው ተላንቃ፣ ተሳንባና ተደምም ሊወሰድ ይችላል፡፡

 

  1. በሽታው እንዴት ይታከማል? ዋናው ህክምና ምልክቶቹ ጋ ያተኮረ ነው፡፡ ለትኩሳቱ የትኩሳት፣ ለሳሉም የሳል መድሃኒት ይሰጣል፡፡ የእስተንፋስ እጥረት ካለበት ሆስፒታል ገብቶ በተለዬ ክፍል መታከም ይኖርበታል፡፡
  2. በተጨማሪም እንደ ጉንፋንና ሌሎችም የእስተንፋስ በሽታዎች ሁሉ የሰውነት ድርቀት ስለሚያመጣ ብዙ ፈሳሽ መውሰድን ይጠይቃል፡፡

 

  1. በሽታውን እንዴት መከላከል ይቻላል? አበው “ታሞ ተመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!” እንደሚሉት ፍቱኑ መድሃኒት መከላክለ ነው፡፡ ችግሩ የውሃ አቅርቦት እንኳ እንደ ሰማይ በራቀበትና በአንድ ጎጆ እስከ አስር ሰው በሚኖርበት አገር ይኸንን በሽታ እንዴት መከላከል ይቻላል የሚለው ነው?

ለሕዝብ ደህንነት የሚጨነቁና ሐላፊነት የሚሰማቸው አገሮች ቫይረሱ ወደ አገራቸው እንዳይገባ በራቸውን ቀርቅረው ዘግተው ተበራቸው የደረሰውንም ተጠርጣሪ ሰው በቂ ጊዜ ወስደው እየመረመሩ ነው፡፡ ዋናው መከላከያ ዘዴ ቫይረሱ ወደ አገር እንዳይገባ ማድረግ ነው፡፡

ቫይረሱ ወደ አገር ተገባና መሰራጨት ተጀመረስ መከላከያ መንገዶቹ ምንድናቸው? አቅም ተፈቀደ መከላከያ ዘዴዎች እነዚህን የመሳሰሉት ናቸው፡፡

  1. በቫይረሱ እንደተበከሉ ታወቁ ወይም ተጠረጠሩ ራስዎን ያግሉ፡፡ እንኳን ለመፈጸም ለማለትም ቢከብድ ተቤተሰቦችዎም ቢሆን ተገልለው እነሱንም ሆነ ያገርዎን ሕዝብ ተመበከል ያድኑ፡፡

ለ. በስልክ ብቻ ከቤተሰብዎም ሆነ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ይነጋገሩ

ሐ. አፍዎን በማፈኛ (ማስክ) ይሰሩ

መ. ሳልዎንና ንጥሻዎን በጨረቅ ወይም በመሃረብ ይገድቡ

ሠ. የመመገቢያም ሆነ ሌሎች እቃዎችን አያጋሩ

ረ. በእጅ እየጨበጡ፣ እየተሳሳሙና እየተቃቀፉ ሰላምታ መለዋወጥን ያቁሙ

ሰ. እጅዎን ደጋግመው በሳሙና ይታጠቡ

ሸ. የተጠቀሙባቸውን እቃዎች በደንብ ይጠቡ

ቀ. የበሽታ ምልክቶችን ይመዝግቡና ለጤና ባለሙያው በስልክ ይንገሩ

በ. ብዙ ፈሳሽ ይጠጡ

በቋንቋዎ እየተረጎሙ ወይም ራስዎ ተመሳስይ መልእክት እየጣፉ መልእክቱን በተለይ በገጠር ለሚኖረው ሕዝብ ያድርሱ፡፡

የህክምና ባለሙያ ተሆኑ እንደ ኤሊ የሚንከረፈፈውን የዓለም ጤና ድርጅት ይተውና ቫይረሱን ለመከላከል የላቦራቶሪ ማግኛ ዘዴን በቀናት ውስጥ ተመፍጠር ጀምሮ ታምረኛ ሥራ በመስራት ላይ ያለውን የአሜሪካ የበሽታ መቋቋሚያ ማእከል (https://www.cdc.gov) ገጥ በየቀኑ ይከታተሉ፡፡

አመሰግናለሁ!

የካቲት ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Don`t copy text!