የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር

የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በዓለም ላይ ለሴቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ በሽታዎች መካከል ስሙ ቀድሞ ይነሳል፡፡ በአብዛኛው በሽታው የሚጠቁ ሴቶች እድሜያቸው ከ23 እስከ 49 ዓመት የሚገኙ ሲሆኑ በዚሁ ዙሪያ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ በ2012 ብቻ በዓለማችን ወደ 528 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በበሽታው ተይዘው ነበር፡፡በዚሁ ዓመት ብቻ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር 266ሺህ የሚሆኑትን የዓለማችን ሴቶች ለሞት ዳርጓል፡፡

የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በምስራቅ እና በመካከለኛው አፍሪካ የተለመደ አስከፊ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓለማችን ውስጥ በዚህ በሽታ ብቻ ከሚፈጠር 10 ሞት መካከል 9 ያህሉ ወይም 87 በመቶ የሚሆነው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ደሃ አገራት ዜጎችን ህይወት የሚያጠፋ ነው፡፡ በመሆኑም በየሁለት ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ምትክ የሌላት የአንዲት የአለማችን ሴት ህይወት ታልፋለች፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 ባለው የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት “WHO” መረጃ መሰረት በታዳጊ አገራት ውስጥ ብቻ ወባ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እንዲሁም የቲቢ በሽታዎች በጣምራ ከሚያስከትሉት ሞት ይልቅ የካንሰር በሽታ የሚያስከትለው ሞት በልጦ ይገኛል፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያም በየዓመቱ ስልሳ ስድስት ሺህ ሰዎች በካንሰር እና ከካንሰር ጋር በተያያዘ በሽታ የሚጠቁ ሲሆን፣ በካንሰር የሚሞቱት 6 በመቶ ናቸው፡፡

የካንሰር ህክምና በአገራችን ውስጥ በስፋት ካለመገኘቱ እና ህብረተሰቡም ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ እጅግ አናሳ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በየጊዜው በርካታ እህቶቻችን ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡ ሆኖም ግን የበሽታውን ምልክቶች ቀድሞ በማወቅ እና በመረዳት እንዲሁም የቅድመ ምርመራ በማድረግ በተለይም የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን መከላከል ብሎም በሽታውን ማዳን ይቻላል፡፡
ለመሆኑ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምንድነው? መንስዔዎቹ እና ምልክቶቹ ምን ምን ናቸው? እንዲሁም ቅድመ ካንሰር ምርመራስ ምንድነው? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ግንዛቤ ሊፈጥሩ ይችላሉ የተባሉት ነጥቦች ከብዙው በጥቂቱ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምንድነው?

ይህ የካንሰር ዓይነት በማህጸን በር ላይ የሚከሰት ካንሰር ሲሆን በአብዛኛው Human Papiloma Virus በሚባል በአይን በማይታይ ተህዋስ የሚመጣ ነው፡፡ ቫይረሱ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ነው፡፡ ይህ በሽታ በአብዛኛው ስር ሳይሰድ ከተደረሰበት በትንሽ ህክምና በአጭር ጊዜ ሊጠፋ የሚችል ሲሆን፣ በአንዳንድ ሴቶች ላይ በሽታው ተደብቆ የማህጸን በር ጫፍ ላይ ተፈጥሯዊ ያልሆነ እድገት እና ለውጥ በማስከተል የማህጸን በር ጫፍ ቅድመ ካንሰር ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡

ለበሽታው መከሰት መንስዔዎች

ዝቅተኛ ኢኮኖሚ እና የአኗኗር ዘይቤ ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ከሚያጋልጡ ችግሮች መካከል በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ ገና በለጋ እድሜ ትዳር መስርተው የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚጀምሩ፣ ከአንድ ሰው በላይ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ፣ በአባለ ዘር በሽታ የተጠቁ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በደም ውስጥ ያለባቸው፣ ሲጋራ የሚያጨሱ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሴቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለዚህ በሽታ ተጋላጭ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ሊከላከሉት የሚቻል በሽታ ቢሆንም፤ ካለው ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ እና ከግንዛቤ እጥረት እንዲሁም ህክምናው በበቂ ሁኔታ ካለመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ የብዙ ሴቶች ህይወት በከንቱ ያልፋል። ይሁን እንጂ ለጤናቸው ቅድሚያ በመስጠት በየጊዜው የቅድመ ካንሰር ምርመራ የሚያደርጉ ሴቶች ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው በእጅጉን ዝቅተኛ እና ችግሩ እንኳ ቢኖር በጧት ይደረስበታል፡፡

የበሽታው ምልክቶች

የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ህመሙ ሲጀምር ምንም አይነት ምልክት አያሳይም። ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ገብቶ ምልክቶች ለማሳየት በርካታ ዓመታትን ስለሚፈጅበት ምልክቶቹን በቶሎ አውቆ ወደ መፍትሄ ለመሄድ ያስቸግራል። ህክምና ሳያገኝ ሲቆይና ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ የሚኖረው ሥርጭት እየበዛ እና እየሰፋ ሲሄድ ግን ምልክቶቹ መታየት ይጀምራሉ። ምልክቶቹ መታየት የሚጀምሩበት ደረጃም በሽታው ከቅድመ ካንሰርነት ወደ ካንሰርነት የሚሸጋገርበት ወቅት ነው። የማህፀን በር ካንሰር መኖሩን ከሚጠቁሙት ዋና ዋና ምልክቶች መካከል ደግሞ የበሽታው ምልክት መደበኛ ባለሆኑ ጊዜያት ህመም አልባ የሆነ ደም ከማህፀን መፍሰስ መጀመር አንዱ ነው።

ለምሳሌ፤ ከመደበኛ የወር አበባ ጊዜ ውጪ፣ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ፣ ከማረጥ በኋላ፣ ብልትን ከታጠቡ በኋላ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም የሚታየው ምልክት መጥፎ ጠረን እና ውሃማ ቀለም ያለው የማህፀን ፈሳሽ መውጣት፣ የጐን፣ የወገብ እና የእግር ህመም ስሜት መሰማት፣ የሽንት ቧንቧ ወይም የፊንጢጣ መድማት፣ የእግር እብጠት፣ እንዲሁም የሽንት ወይም የሰገራ ማምለጥ (fistula) ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የማህፀን በር ጫፍ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ምንድነው?

የማህፀን በር ጫፍ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ዕድሜያቸው ከ23-49 ዓመት ለሆኑ ማናቸውም ሴቶች የሚደረግ ምርመራ ነው፡፡ ምርመራው እጅግ ቀላል እና አስተማማኝ ከመሆኑም ሌላ ውጤቱንም ወዲያውኑ ለማወቅ ያስችላል፡፡ በመሆኑም ይህን ምርመራ ያካሄደች ሴት በማህፀን በር ጫፍ ላይ ካንሰር ከመከሰቱ በፊት አመላካች የሆኑ ለውጦች መኖራቸውን ለማወቅ ትችላለች ማለት ነው፡፡

የማህፀን በር ጫፍ ቅድመ ካንሰር ሊድን ይችላልን?

የማህፀን በር ካንሰርን አስቀድሞ በሚደረግ ጥንቃቄ እና ምርመራ መከላከል ይቻላል። ለበሽታው መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በማስወገድም ለበሽታው ያለውን ተጋላጭነት መቀነስ ይቻላል። የቅድመ ካንሰር ምርመራን በማድረግ የማህፀን በር ካንሰር ከመከሰቱ ከአስር ዓመት በፊት አስቀድሞ ማወቅ የሚቻል ሲሆን በወቅቱ ከተደረሰበት እንዲሁም በሐኪም የሚታዘዝ ህክምና እና መድሃኒት በአግባቡ ከተወሰደ ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ መዳን ይቻላል፡፡

ሆኖም በሽታው ቀድሞ ካልታወቀ እና ለረጅም ጊዜ ሥር ከሰደደ ሕክምናውም የዚያኑ ያህል አስቸጋሪ እና የመዳን እድልም የጠበበ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የትኛዋም የግብረሥጋ ግንኙነት የምታደርግ ሴት ከ23 እስከ 49 ዓመት የሆነች ሴት የቅድመ ካንሰር ምርመራውን በማድረግ ራሷንም ሆነ ቤተሰቧን ከአደጋ ልትጠብቅ ይገባል፡፡

አገራችንም የ10ኛው የየማህፀን፣ የፕሮቴስት እና የጡት ካንሰርን ከአፍሪካ ለማጥፋት የተካሄደውን ጉባዔ በአዲስ አበባ በቅርቡ ማስተናገዷ እና የተከበሩ ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ ይህንኑ ጉዳይ ሥራዬ ብለው ይዘው ከግብ ለማድረስ በጽህፈት ቤታቸው ሰፊ ርብርብ ማድረጋቸው የቅድመ መከላከሉ አካል ነው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Don`t copy text!