Prostate cancer/ፕሮስቴት ካንሰር

ፕሮስቴት ካንሰር:- አልፎ አልፎ እየጠፋ የሚመጣ የእብጠት ምልክት ምንድን ነው?

ከአንድ ዓመት በፊት ሽንት መሽኛዬ አካባቢ አልፎ አልፎ እየታየኝ የመጣው ምልክት ግራ መጋባትን ጭንቀትን ስላስከተለብኝ ነው፡፡ በቆለጤ ፍሬ ላይ አልፎ አልፎ እየጠፋ የሚመጣ የእብጠት ምልክት ከጀመረኝ ጊዜ ጀምሮ ሽንቴ ቶሎ ቶሎ ይመጣል፡፡ እብጠቱ የራሱን ወቅት ጠብቆ ቢጠፋም ተመልሶ ይመጣል፡፡ አሁን ግን በራሱ ጊዜ ተመልሶ ይጠፋል ብዬ ብጠብቅም በጣም ቆየብኝ፡፡ ከዚህ ባለፈ ሌሊት ሌሊት ሽንትም ጀማምሮኛል፡፡ ሆኖም እየተቆራረጠ ችግር ሆኖብኛልና ከምንም በላይ ግን አለመረጋጋት ፈጥሮብኛል፡፡ ወደ ህክም ብሄድም ኢንፌክሽን ነው ተብዬ መርፌ ብቻ ታዘዘልኝ፡፡ ሆኖም አማራጭ ስላጣሁ ችግሬ ምን እንደሆነ አስረድታችሁኝ ማድረግ የሚገባኝን ጥንቃቄ ካለ እንድትነግሩኝ እለምናችኋለሁ፡፡
አምሳሉ

Prostate Cancer
ውድ አንባቢያችን በህክምና ስለተሰጠህ ምክንያት ብትገልፅልንም ምን እንደሆነ ዘርዘር አድርገህ አላብራራህልንም፡፡ ሆኖም ችግርህን ስንመለከተው ከፕሮስቴት እጢ ጋር ተመሳሰለብን፡፡ እኛ ስለ ፕሮስቴት እጢና ካንሰር ምንነት እናስረዳሃለን፡፡ ከዛ ባለፈ አንተ በኩላሊትና ተመሳሳይ አካላቶች ህክምና ልዩ እስፔሻሊስቶች ጋር እንድትሄድ በግላችን እንጠቁምሃለን፡፡

የፕሮስቴት እጢ በወንዶች ብቻ የሚገኝ የሰውነት አካል ሲሆን ከወንዶች የስነ ተዋልዶ አካላት ውስጥ አንዱ በመሆን ይጠቅማል፡፡ ይህ እጢ የሚገኘው ከሽንት ፊኛ በታች ሲሆን የሽንት ትቦ የመሀከለኛውን ክፍል ዙሪያ ከቦ ይገኛል፡፡ ይህ የኦቾሎኒ ያክል መጠን ያለው የፕሮስቴት እጢ ከዕድሜ ጋር መጠኑ እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን በተግባሩም ለስፐርም የሚሆነውን ፈሳሽ ከሚያመነጩ የሰውነት አካል ውስጥ አንዱ ሆኖ ይገኛል፡፡
ለዛሬ የምንመለከተው ዋናው ርዕስ የፕሮስቴት እጢ በሚያድግበት ወቅት የሚከተለውን ሁለት አይነት ችግር ነው፤
1. የካንሰር ምልክት/ጠባይ የሌለው የፕሮስቴት እጢ ማበጥ/ማደግ (Benign prostatic Hypertrophy) እና
2. የፕሮስቴት ካንሰር
የካንሰር ምልክት/ጠባይ የሌለው የፕሮቴስት እጢ ማበጥ/ማደግ Benign prostatic Hypertrophy
ይህ ካንሰር የማያስከትል የፕሮስቴት እጢ ማበጥ ሲሆን መሰረታዊ ምክንያት በውል ባይታወቅም በዕድሜ ለውጥ የሚከተሉ የሆርሞኖችን መለዋወጥ ተከትሎ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል፤ በዚህም ሳቢያ በአብዛኛው የዚህ ችግር ተጠቂዎች የሆኑት ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች ናቸው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የፕሮስቴት እጢ በሽንት ትቦ ዙሪያ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን መጠኑ በጨመረ ቁጥር ቀስ በቀስ የሽንት ትቦን የመጫንና በዚህም ሳቢያ የማጥበብ ብሎም ጨርሶ የመዝጋት ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ የሽንት ፊኛ በዚህ ጠባብ ትቦ ሽንትን ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት የሽንት ፊኛ ጡንቻ ማደግና መጠንከር ይከተላል፡፡ ይህም የሽንት ፊኛ ውስጥ ያለው የሽንት መጠን ተሟጦ የመውጣት ስሜት ከማስከተሉም በላይ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንና ለሽንት ቧንቧ ጠጠር መፈጠር ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ሁኔታዎች እየተባባሱ በመጡ ቁጥርና ጊዜው በረዘመ ቁጥር የኩላሊት መጎዳትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

ሊከተሉ የሚችሉ ምልክቶች/የህመም ስሜቶች

የፕሮስቴት እጢ የማደግ ስሜትን ማስከተል የሚጀምረው የሽንት ትቦ ላይ ጫና በማስከተል ሽንት እንዳይወጣ መከልከል ሲጀምር ነው፡፡
– በመጀመሪያ ደረጃ ሽንት የመሽናት ስሜት ከመጣ በኋላ መሽናት ለመጀመር ጊዜ መፍጀት፣
– ሽንት ጨርሶ ያልወጣ ያልወጣ መስሎ መሰማት፣
– ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣትና ማጣደፍ፤
– በሌሊት ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ ከእንቅልፍ ለሽንት መነሳት፤
– ሽንት በሚሸኑበት ወቅት መጠኑ መቀነስና መቆራረጥ እንዲሁም ለመሽናት መታገል፤
– ሽንት ሸንተው ከጨረሱ በኋላ የመንጠባጠብ ሁኔታ፤
– በአንድ አንድ ሁኔታ ሽንት ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ መፍሰስ፤
– በሽንት ትቦና ፊኛ አካባቢ ያሉት ትናንሽ የደም ስሮች ሽንት ለማስወጣት በሚደረገው ግፊት መበጣጠስና በሽንት ውስጥ ደም የመከሰት ሁኔታ፤
– የሽንት ትቦ ከነአካቴው የተዘጋ እንደሆነ ደግሞ ፊኛ ከመጠን በላይ መወጠርና በታችኛው የሆድ ክፍል ከፍተኛ የህመም ስሜት መሰማት፤
– የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የተከሰተም እንደሆነ በመሽናት ወቅት የማቃጠል ስሜት በብልት ላይ መሰማትና እንዲሁም የሰውነት ትኩሳት መከተል ሊታዩ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ግዴታ በአንድ ላይ ይከሰታሉ ማለት ባይሆንም በእነዚህ ጥቂት ስሜቶች ብቻ ቢኖሩም የዚህ ችግር ምልክት ለመሆን ይበቃሉ፡፡ እነዚህ ስሜቶች በሚኖሩን ጊዜ በምን ማወቅና ማረጋገጥ ይቻላል የሚለውን ከታች የምንመለከተው ይሆናል፡፡

ፕሮስቴት ካንሰር

የፕሮስቴት ካንሰር በወንዶች ላይ በብዛት የሚታይ ሁኔታ ቢሆንም እንደ አብዛኛው የካንሰር አይነቶች መንስኤው በውል አይታወቅም፡፡ በፕሮስቴት እብጠት ሳቢያ በቀዶ ጥገና ከሚወገዱ የፕሮስቴት እጢዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚገኘው የፕሮስቴት እብጠት ካንሰር መሆኑን ያመለክታል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ የፕሮስቴት ካንሰር ቀስ በቀስ የሚያድግና የሚሰራጭ እንደመሆኑ መጠን አስከፊ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ምንም አይነት ስሜት ላያስከትል ይችላል፡፡
ሊከተሉ የሚችሉ ምልክቶች/የህመም ስሜቶች
ከላይ እንደተጠቀሰው የፕሮስቴት ካንሰር አደገኛ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ በአብዛኛው ጊዜ ምንም አይነት ምልክት ባያስከትልም በፕሮስቴት እብጥት ሳቢያ ሊከተሉ የሚችሉ ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነገር ግን የፕሮስቴት ካንሰር መሰራጨት ከጀመረ በኋላ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንደ አጥንት፣ ኩላሊት ብሎም ወደ አንጎል በመሰራጨት የተለያየ አይነት የህመም ስሜቶችና ሁኔታዎችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ይህንን ችግር በምን ማረጋገጥ ይቻላል?
አንድ ሰው ከላይ የተጠቀሱት ስሜቶች በሚሰሙበት ወቅት ወይም የጤና ባለሙያ ይህንን ሁኔታ በሚጠራጠርበት ወቅት ሊደረጉ ከሚገባቸው ምርመራዎች ውስጥ፤
– በፊንጢጣ በኩል ጣትን በማስገባት የፕሮስቴት እጢው ማበጥ አለማበጡንና፣ ከዚያም በተጨማሪ አስፈላጊ የሆኑ የመለያ ነጥቦችን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
– ከዚህም በተጨማሪ አልትራሳውንድ ምርመራ በማድረግ ችግሩ መኖሩንና ከሆነም ደግሞ ካንሰር የመሆንና ያመሆኑን ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ መገመት ይቻላል፡፡
– የፕሮስቴት ዕጢ ማደጉንና እንዲሁም ካንሰር የመሆን ዕድሉን ሊነግረን የሚችልም የደም ምርመራ እንደመኖሩ ይህንን ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ እንዲያውም ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶች ላይ ይህንን የደም ምርመራ በየዓመቱ ማድረግና አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡
– ከፕሮስቴት ዕጢ ናሙና በመውሰድ የእጢውን ሁኔታ ማረጋገጥም ተመራጭ የሆነውና እርግጠና ሁኔታውን ሊነግረን የሚችል የምርመራ አይነት ነው፡፡
– የፕሮስቴት ካንሰር የተሰራጩ እንደሆነም እንደየአስፈላጊነቱ የተጠቃውን የሰውነት አካል የተለያዩ ምርመራዎች ማድረግ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ይረዳል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ስሜቶች የሌላ ህመም መገለጫ ሊሆኑ እንደመቻላቸው አስፈላጊውን ምርመራ እንደየአስፈላጊነቱና በደረጃ ማድረግ መሰረታዊ ነው፡፡ ስለዚህም ትንሽ ነው ብለን ጊዜ የሰጠነው የፕሮስቴት ዕጢ ችግር ለባሰ ሁኔታ ሳያጋልጠን በጊዜ ህክምና ብንወስድበት ስለ ህመሙም አውቀን የቅድመ ጥንቃቄ ወይም የመከላከል እርምጃ ብንወስድ መልካም ነው፡፡

Most Popular

To Top