ሚግሪን (Migraines)

ሐኪሞች Migraine Headache (የራስ መርዘን) አለብሽ ብለውኛል፤ ለመሆኑ ምን ዓይነት በሽታ ነው?

ስሜ ሳምራዊት ቢ ይባላል፡፡ 35 ዓመቴ ነው፡፡ ምክንያቱን ባላውቅም በአብዛኛው ጊዜ ግማሹን የጭንቅላት ክፍሌን ያመኛል፡፡ ህመሙን ተከትሎም የማቅለሽለሽና የማስመለስ ስሜት ይሰማኛል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አንድ የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ አድርጌያለሁ፡፡ የምርመራው ውጤት ግን ግራ አጋብቶኛል፡፡ ሐኪሙ ያለኝ Migraine Headacheየሚባል የራስ ህመም አለብሽ ነው፡፡ ዘሃበሻዎች ለመሆኑ የራስ መርዝን ምን አይነት በሽታ ነው? በሽታው ዘላቂ መፍትሄስ አለው ይሆን?
ሳምራዊት ቢ

Migraine-Headache tenaadam
የዶ/ር ዓብይ ምላሽ፦ ከሁሉም አስቀድመን መፍትሄ ፍለጋ ወደ ዝግጅት ክፍላችን ደብዳቤ በመፃፍሽ ደስ ብሎናል፡፡ እናሰመግናለን፡፡ ወደ ጥያቄሽ ስንመለስ Migraine Headache ወይም በአማርኛ አጠራሩ ‹‹የራስ መርዘን›› በመባል የሚታወቀው በሽታ ከራስ ምታት የህመም አይነቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ የጤና ችግር በብዙ አገሮች በብዛት የሚታይ ችግር ነው፡፡ አገራችንን ጨምሮ በዓለም ላይ ካሉ ህዝቦች 15 በመቶ ሴቶችና 6 በመቶ ወንዶች በችግሩ ይጠቃሉ፡፡
በሽታው በባህሪው በህፃናትና በወጣቶች ላይ አዘውትሮ የሚከሰት ቢሆንም በተለየ ሁኔታ ግን ከ30 እስከ 39 ዕድሜ ክልል ባሉ ሰዎች ዘንድ በብዛት ይታያል፡፡ ነገር ግን ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ በዚያው መጠን የጤና ችግሩ ይቀንሳል፡፡ በዘር የመተላለፍ እድሉም ከ40 እስከ 50 በመቶ እንደሚደርስ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ውድ ሳምራዊት የራስ መርዘን በሽታ ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም የመሄድና የመምጣት ባህሪ ያለው ሲሆን ለስሜትና ለአካባቢያዊ ሁኔታዎች በቀላሉ ተጋላጭ ይሆናል፡፡ በዚህም ሳቢያ አንዳንድ ሁኔታዎች በተለይም የፀሐይ ነፀብራቅ፣ ደማቅ ብርሃን፣ ድምፅ፣ ረሃብ፣ አዕምሮአዊና አካላዊ ጤናዎች እንደዚሁም ሴቶች የወር አበባ ሲመጣ፣ አልኮል መጠጦች፣ ጭስ፣ ከባድ የአየር ሁኔታ፣ የእንቅልፍ ማጣትና መብዛት ‹‹የራስ መርዘን›› የተባለውን በሽታ በተደጋጋሚ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

የዚህ አይነቱ የጤና ችግር አመጣጥ ጥልቅና ውስብስብ ሁኔታዎች ያሉት ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሽታውን አስመልክተው በተደረጉ ጥናቶች የተደረሰበት መንስኤ ጭንቅላት ውስጥ ያሉ የነርቭ ክሮች መዛባት በጭንቅላት ላይ የሚፈጥሩ ውስጣዊና ውጫዊ ለውጦች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በሽታው የራሱ የሆኑ ህመም ነክ ምልክቶች ያሉት ነው፡፡ ምልክቶቹ በ3 ደረጃዎች ተከፍለው ይታያሉ፡፡ ቀጥለን እናያቸዋለን፡፡

ቅድመ ራስ ምታት
ስሜቶች፡- በዚህ ደረጃ የሚስተዋሉ ህመም ነክ ምልክቶች መካከል የእይታ መለወጥ፣ የፊት ወይም የእጅ አካባቢ መደንዘዝና የመጠዝጠዝ ስሜቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ራስ ምታት ደረጃ ላይ ሲደርስ
በአብዛኛው ግማሹን የጭንቅላት ክፍል ከፍሎ ህመም የሚሰማ ሲሆን ህመሙንም ተከትሎ የማቅለሽለሽና አልፎ አልፎም የማስመለስ ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡ በተጨማሪም ብርሃንና ድምፅን የመጥላት ስሜት ይንፀባረቃል፡፡ እንዲህ ያለው ምልክት ከ4፡00 ሰዓት በላይ እና ለቀናት ሊዘልቅም ይችላል፡፡

ድህረ ራስምታት

ዋናው የራስ ምታት ስሜት ይቆምና ድካምና ቅፅበታዊ የጭንቅላት እንቅስቃሴዎች ራስ ህመሙን በድጋሚ ሊቀሰቅሱት ይችላሉ፡፡ ከላይ ከተገለፁት ህመም ነክ ምልክቶች በተጨማሪ ግማሽ አካል ሽባ የመሆንና ራስ የመሳት ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነገር ግን ወደ ጤናማነት የመመለሱ ሁኔታ አለ፡፡
የ Migraine Headache በሽታ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ቀደም ሲል የዘረዘርናቸው ህመም ነክ ምልክቶች ከበቂ በላይ አመላካች ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ ምልክቶች ከሌሎች የጭንቅላት ውስጥ በሽታዎች ጋር የመመሳሰል ባህሪ ያላቸው በመሆኑ ይህን ሁኔታ ለማጣራት የሲቲ ስካን ወይም ደግሞ MTR ምርመራ ሊደረግ ይችላል፡፡ የህክምናውን ውጤት መሰረት አድርጎ ለሚካሄደው ህክምና የበሽታው ተጠቂዎች ንቁ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሽታው እንዳለበት ደረጃ እና አጣዳፊነት መጠን ለመፍትሄ የሚሰጡ መድሃኒቶች አሉ፡፡ የመድሃኒቶቹ አይነት ከማስታገሻ ጀምረው እስከ ከፍተኛው ደረጃ የሚደርሱም ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ጠቃሚ የሚሆነው ችግሩን አስቀድሞ መከላከሉ ይሆናል፡፡ የጤና ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን ለይቶ ማስወገድ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን መከተልና አካላዊ እንቅስቃሴን አዘውትሮ መስራት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል የተመጣጠነ እንቅልፍ መተኛት፣ ከአልኮልና ከአነቃቂ እፆች ራስን መጠበቅ ከችግሩ ለመፅዳት መሰረታዊ ጉዳይ ይሆናል፡፡ እነዚህ የመከላከያ ስልቶችን በመጠቀም Migraine Headacheን (የራስ መርዘን) በሽታ እንዳይቀሰቀስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ውድ ሳምራዊት የበሽታውን ምንነትና መከላከያ መንገዱን ተገንዝበሽ መፍትሄውን ከፈለግሽ ከችግርሽ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆን ትችያለሽ ለማለት እንወዳለን፡፡

Most Popular

To Top