ስነ-ልቦና

ላፈቀርካት ሴት ያለህን የፍቅር ስሜት እንዴት መግለፅ ትችላለህ?

loveከቅድስት አባተ
ፍቅርም ሆነ መፈቃቀር ለሰው ልጆች በሙሉ ያለመድልዎ የተሰጠ ፀጋ ነው፡፡ ፍቅር የሁላችንም አካል ነው፡፡ በፍቅር የተሞላና የተሻለ የፍቅር ኑሮ እንዲኖረንም የብዙዎቻችን ምኞት ነው፡፡ ታዲያ የእኛው ሆኖ ሳለ ብዙዎቻችን ፍቅርን አንቀበለውም ወይም እናባርረዋለን፡፡ ፍቅርንመ ሰጥተን እንዳንቀበል ብዙዎቻችን ማዕቀብ የተደረገብን ይመስለናል፡፡ ፈላጊና ተፈላጊ ሳይገጣጠሙ ሲቀሩ ደግሞ ፍቅር እንደተራብን ልንቆይ ግድ ይለናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የፍቅር ጥያቄ እንዲያቀርቡ የሚገደዱት ወንዶች በመሆናቸው ይህን የፍቅር ስሜት ለመግለፅ በህይወታቸው ውስጥ ትልቁ የቤት ስራ ይሆንባቸዋል፡፡ ነገር ግን የፍቅር ስሜታችንን ለመግለፅ የሚኖረን አካሄድ ከልጅነት አስተዳደጋችን ጋር ተያይዞ የሚመጣና ውስጣችን ተቀርፆ ባለው መልኩ ለፍቅር በደረስንበት ዕድሜ ላይም እንደ ችግር ወይም በተቃራኒው እንደ ጥሩ ነገር ልናንፀባርቀው እንችላለን፡፡
ለዚህም ነው አስቀድመን ፍቅር የሚለውን ቃል ራሱ ስናስብ በአዕምሯችን ሀሳባዊ የሆነ ነገር እንስላለን፡፡ እዘህ ላይ ልናይ የሚገባን ነገር ልጆች እያለን ምንም የምንስለው ሀሳባዊ ነገር በፍቅር ዙሪያ ስላልተነገረን ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ብቻ ከዕድገት ለውጣችን ጋር በሚፈጠረው ፍቅር ልባችንን ክፍት አድርገን እንቀበላለን፤ ለማጣጣምም እንሞክራለን፡፡ በሀሳባዊ ስዕል ውስጥ በቅፅበት የሳልነውን ፍቅር ለማግኘት ደግሞ ስለሚከብደን እየተፈቀርን እንኳን ፍቅርን እንራባለን ወይም እያፈቀርን እንኳን የተፈቃሪን ልብ ማግኘት ያስቸግረንና ፍቅርን እንራባለን፤ ያለመገጣጠም ማለት ይህ ነው፡፡ እንደ ልጅነታችን ቢሆን ኖሮ እኮ ሰዎች ትኩረት ስለሰጡን ወይንም ልናገኘውና የእኛ ልናደርገው የምንፈልገውን ነገር አንድ ሰው ሲያደርግልን የፍቅር ስሜቱ በቀላሉ ይገባና ተፈቀርን ብለን እናስብና የፍቅር ረሃባችንን እናስወግድ ነበር፡፡ ያ ማለት ትኩረት የሰጠን ወይንም የምንፈልገውን ነገር የሰጠን ሁሉ አፍቃሪያችን እንደሆነ እናስብ ነበር ማለት ነው፡፡ ታዲያ አድገን የእኛ እንዲሆን የምንፈልገው ፍቅር እንደ ልጅነታችን ከብዙዎች መምጣቱን ሳይሆን እኛው ካፈቀርነው ሰው ብቻ ምላሹን መጠበቃችን ሁለቱን የተለያዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ለማፍቀር በደረስንበት ዕድሜ ወቅት አፍቅሮ እንዲፈቀሩ መፈለግ ወይም ለፍቅር መጠያየቅ ተፈጥሯዊ እንደሆነ ማወቅ የግድ የሚሆነው፡፡ እንደ ተፈጥሮነቱ ፍቅርን ስንፈልግ ደግሞ የህይወት አጋርን የመፈለግ ጉዞ ውስጥ እንገባለን፡፡ በዚህ የመፈላለግ ጉዞ ውስጥ ታዲያ የሁለቱም ተፈላላጊዎች መገጣጠም ይኖርና ነገሩ ቀላል ሊሆንላቸው ይችላል፡፡ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ፈላጊው ራሱ አፍቃሪ ይሆንና ተፈቃሪዋ ብዙም መፈቀሯን ሳታውቅ በፍለጋ ብቻ ረዥም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህ በተለይ ወንዶች ላይ በብዛት የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ለዚህ ትልቁ ምክንያት ደግሞ በብዙ ልማዶችና እምነቶች የፍቅር ጥያቄን ማቅረብ ያለበት ወንድ ነው የሚል እሳቤ ሰርጾ ስለነበር ነው፡፡ ይህ አመለካከት በተወሰነ መልኩ የተቀየረ ቢሆንም በብዛት ግን አሁንም ሴቷ እያፈቀረችውም ቢሆን የፍቅር ጥያቄው ከወንዱ እንዲመጣ የመፈለግ ዝንባሌ አለ፡፡ ይህን ሁኔታ ወንዶች አቅልለውት በመመልከት ፍቅራቸው የሚበልጥባቸው ከሆነ ፍርሃታቸውን አስወግደው የፍቅር ጥያቄያቸውን አስወግደው የፍቅር ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ከተሳካላቸው እኮ ከሴቷ የበለጠ የአሸናፊነት ስሜት የሚሰማቸው ወንዶቹ ይሆናሉ፡፡ ምክንያቱም ረዥሙን ሂደት የተጓዙትና ድል ያደረጉት እነሱ ናቸውና፡፡ ታዲያ ወንዱ ከራሱ የፍቅር ስሜት በመነሳትና ውስጡን በማዳመጥ ይጀመርና ማንነቷን ከለየ በኋላ እንዴት ፍቅሩን ሊገልፅላት እንደሚችል ማወቅ አለበት፡፡
ገና ስታያት ልብህ የደነገጠላትን ሴት እንደምንም ብለህ ማናገር አለብህ፡፡ በደንብ ለመግባባት እንድትችሉ ደግሞ በተቻለህ አቅም መንገድ ላይ እየሄዳችሁ ከሆነ የተገናኛችሁት መንገድህን ቀይረህ ከእሷ ጋር በመሄድ ጨዋታችሁን አራዝም፣ በታክሲም ውስጥ ከሆነም እንዲሁ መንገድህን አሳልፈህ በመሄድ በተቻለህ አቅም በደንብ ለመግባባት የሚያስችላችሁን ረዘም ያለ ወሬ በማውራት ተጨዋወቱ፡፡ ስትለያዩም ሌላ ጊዜ እንድትገናኙ ስልክ ቁጥሯን ተቀበላት፡፡ አንድ ሶስት ቀን በስልክ ከተገናኛችሁ በኋላ አንድ የእረፍት ቀን ተገናኝታችሁ ሻይ ቡና እንድትሉ ጠይቃት፡፡ በመቀጠልም የምትገናኙበትን እያንዳንዷን ቀን ከፋፍላቸውና ማንነቷን በደንብ የምታውቅበት አንተም ማንነቷን የምትገልፅበት የፍቅርንም ስሜት የምትረዳበት አድርጋቸው፡፡ እነዚህን በግንኙነታችሁ ተከታታይ ቀናት ምን እንደሚመስሉ እናያቸዋለን፡፡
1. የመጀመሪያ ቀን ግንኙነት
የመጀመሪያ ቀን ስትገናኙ ስለ ስራዋ፣ በስራ ቦታና ስላጋጠማት ነገር፣ ስለ ቤተሰቦቿ እናም ከፍቅር ውጭ ስለሆኑ ሌሎች ጉዳዮች አንስታችሁ ተወያዩ፡፡ በመጀመሪያ ግንኙነታችሁ ከፍቅር ውጭ በተለመዱ ጉዳዮች ላይ መነጋገራችሁ ሳትጨናነቁ ዘና ብላችሁ እንድታወሩ ይረዳችኋል፡፡ ስታወሩ ታዲያ በደረቁ ሳይሆን የተለያዩ ቀልዶችን እያነሳህላት አስቃት፡፡ በጨዋታ የታበ ቆይታችሁ ደስ የሚል ጊዜን እንድታሳልፉ ከማድረጉም በላይ አንተ የማታጨናንቅ ቀለል ያልክ ሰው እንደሆንክ ስለምትረዳ እሷም ነፃነቷን ያገኘች ያህል እንዲሰማትና እንድትጫወት ታደርጋታለህ፡፡ እዘህ ጋር መጠንቀቅ ያለብህ ነገር ከእሷ የበለጠ ብዙ አታውራ፣ ለእሷ ሰፊውን ጊዜ ስጣትና አንተ ብዙውን ጊዜ አድማጭ ሆነህ ተገኝ፡፡ የሚያዳምጣትን ሰው በማግኘቷ በጣም ደስ ይላታል፤ ለአንተም ቦታና ክብር ትሰጥሃለች፡፡ ይህን ማድረጋችሁ ደግሞ አንተ ብቻ ሳትሆን እሷም ካንተ ጋር በድጋሚ ተገናኝታ የምታወጉበትን ቀጣይ ቀን እንድትናፍቅር ያደርጋታል፡፡ ስለ ቀጣይ የመገናኛ ቀናችሁም ትንሽ ተባባሉ፡፡ ነገር ግን የግድ በዚህ ቀን ካልሆነ ብላችሁ አትወስኑ፡፡ መደዋወል እንደምትችሉ ተማምናችሁ ተለያዩ፡፡ ስትለያዩ ቢቻል እስከተወሰነ መንገድ ዎክ እያደረጋችሁ ብትሄዱ ወይም ቤቷ ልትደርስ ግማሽ መንገድ እስኪቀራት ድረስ አብራችሁ በታክሲም ብትሄዱ፤ ያለበለዚያ በትራንስፖርት አሳፍረሃት ብትመለስ የመሳሰሉትን እንደ አማራጭና እንደ ሁኔታዎች እያየክ መፈፀም ከቻልክ አንድ ትልቅ ማህተም መተህ እንደላካት ልትቆጥር ይገባሃል፡፡
2. የሁለተኛ ጊዜ ግንኙነት
በስልክ ጥሩ የሆኑ አስደሳች ንግግሮችን ካደረጋችሁ በኋላ ብዙም ሳትርቁ ለሁለተኛ ጊዜ የምትገናኙበትን ቀን ተነጋግራችሁ ተቀጣጠሩ፡፡ ታዲያ ለሁለተኛ ጊዜ ለመገናኘት ስትቀጥራት እንደመጀመሪያ ጊዜያችሁ አነስ ያለ ቦታ ወይም ካፌም ሳይሆን ሬስቶራንት ቢሆን የምትጋብዛትም ሻይ ቡና ሳይሆን ምሳ ወይም እራት መሆን አለበት፡፡ ስትገናኙ አለባበሷንና ስብዕናዋን ሁሉ አድንቅላት፡፡ ታዲያ አንተም የራስህን ስብዕና የሚጠብቁ አለባበስና አቀራረብ ይዘህ ተገኝ፡፡ ጋባዡ አነተ ብትሆንም የምትፈልገውን ነገር እንድታዝ ነፃነቷን ስጣት፣ ካላወቀችውም አሪፉን ነገር አስረዳትና የተሻለውን እንድትመርጥ አድርጋት፡፡ በዚህ ቀን የሚኖራችሁን ሰፊ ሰዓት ስለግል ሕይወታችሁ በስፋት በማውራት እየተጨዋወታችሁ አሳልፉ፡፡ በግንኙነታችሁ መቀራረብ ውስጥ ውስጧንም እያጠናህ መሄድህን እንዳትረሳ፡፡ የበላችሁት የጠጣችሁት ነገር እንደተመቻት ጠይቃት ሌላ ተጨማሪ ነገር የምትፈልግ ከሆነም እንድታዝ አድርግ፡፡ የሁለተኛ ቀን ውሎዎቹ በጥሩ ሁኔታ ከተጠናቀቁ በድጋሚ ሌላ ቀን ለመገናኘት እንደምትቀጣጠሩ አሳውቃት፡፡ የምትቀጣጠሩ ቀን ግን ከተለያያችሁበት ጊዜ በጣም የረዘም መሆነ የለበትም፡፡ ያሳለፋችሁት ጣፋጭ የሆኑ ጊዜያቶች ከአዕምሯችሁ ብዙም ሳይጠፋ ሳትርቁ ለመገናኘት ሞክሩ፡፡ ታዲያ ቀጠሯችሁ ከተሳካ አሁንም በሬስቶራንት ውስጥ መሆኑን ተነጋገሩ፡፡ ወጪ ለመቀነስ ብለህ ወደኋላ ተመልሰህ ካፌ ውስጥ ወይም የወረደ ቦታ ለመቀጣጠር አትሞክር፡፡ ከእንግዲህ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ የሚያስብልህ ምንም ነገር የለም፡፡ የዚህን ቀን ውሏችሁን አጠናቃችሁ ከመለያየታችሁ በፊት ወንድ እንደመሆንህ ነገሮች ከአንተ አፍ ቅድሚያ ይጠበቃሉና በቆይታችሁ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍህን ንገራት፡፡ እሷን በማግኘትህና አንተን አክብራ ከአንተ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ፈቃደኛ ሆና በመገኘቷ በጣም ደስ እንዳለህም አሳውቃት፡፡ እሷን ሁሌ ብታገኛት እንኳን እንደምትደሰት ንገራትና ቶሎ ቶሎ እንደምትደውልላት በመግለፅ ለወደፊቱ ስሜትህን በቀላሉ ለመግለፅ እንዲያመችህ ዳር ዳር ማለት ትጀምራለህ፡፡ እንደተለመደው ከሸኘሃት በኋላ በንጋታው ደውልላት ትናንተ በጣምጥሩ ጊዜ እንዳሳለፋችሁ ንገራት የእሷንም ስሜት ጠይቃትና ቀጣዩ ስራህን ፍቅር ፍቅር እያሰኘህ ለማስኬድ ልታስብበት ተዘጋጅ፡፡
3. የሶስተኛ ቀን ግንኙነት
በዚህ ጊዜ ዕድለኛ ከሆንክ ራሷ ደውላ ባለፈው ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፈች ገልፃልህ በድጋ እንድትገናኙ ትጠይቅሃለች፡፡ ይህን ካደረገች ጥልቅ የሆነ ስሜት በውስጧ እንደተፈጠረባት ያሳያል፡፡ ለአንተም የምትመችህ አይነት ሴት መሆኗን ካረጋገጥክ የፍቅር ጥያቄውን ማቅረብ ቀላል ሊሆንልህ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ምንም ነገር አላለችም ማለት ግን ምንም ስሜት የላትም ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ስሜቷን ለመግለፅ ተቆጥባ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ስልክ ደውለህ ካነጋገርካት በኋላ ስሜቷን ስላልገለፀች መክፋትህን ሳታስነቃ ሌላ ቀን እንደምትደውልልለት ነግረህ ተሰነባበታት፡፡ በተቻለ አቅም ለሶስተኛ ጊዜ እንድትገናኙ እንደምትፈልግ ራሷ እስክምትገልፅልህ ድስ ስልክ እየደወልክ ብቻ ጠብቅ፡፡ ነገር ግን ስሜቷን እንድትገልፅ ፈፅሞ መገፋፋት የለብህም፡፡ ምክንያቱም ከተነቃብህ ውስጧ ቶሎሊረበሽ ይችላልና እንዳማረህ ይቀራል እንጂ ትንፍሽ አትልልህም፡፡ ከዚህም አልፎ ይህ የችኩልነት ባህሪ ሊያስጠላት ይችላል፡፡ ሶስተኛው ቀን በጣም ወሳኝ እንደሆነ አስብና በስልክ ደስ የሚሉ ወደ ፍቅር የሚያመሩ ወሬዎችን በቀልድ መልክ አውራት፡፡ በሞባይልም ከሆነ ደስ የሚሉ ፍቅርን ሊጠቁሙ የሚችሉ ነገር ግን በጣም ፍቅርን በግልፅ የሚያሳዩ ሆነው ያላፈጠጡ መልዕክቶችን (SMS) ላክለት፡፡
የእሷ መልስ ላይ ብዙ ትኩረት አታድርግ ወይም አትጠባበቅ፡፡ የሶስተኛው ቀን ግንኙነታችሁ በስልክ ረዥም ሰዓትን የወሰደ ከሆነ ከላይ በተገለፀው መልኩ ነገሮችን ግለፅላት፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ጠብቀህ ካልሳካልህ በቀጣይ ቀናት ራስህ እንድትገናኙ ትቀጥራትና በሌላ ጊዜ ደግሞ እሷ እንድትቀጥርህ እድል ስጣት፡፡ በዚህ ቀን ስትገናኙ ግን ሆን ብለህ ወሬያችሁ ሁሉ በፍቅር ዙሪያ ብቻ እንዲሆን በማድረግ ያላትን ስሜት ለማወቅ ሞክር፡፡ ላንተ የፍቅር ስሜት እንዳላት ከሁኔታዋ ለማወቅ ከቻልክ አንተም ያለህን ስሜት ዳር ዳር እያልክ ግለፅላትት፡ ለምሳሌ ከሰውነቷ ክፍል ፀጉርሽ ወይም ጥርስሽ ያምራል እያልክ፣ የፊትሽ ቆዳ ደግሞ እንዴት ይለሰልሳል እያልክ እየነካካሃት ግለፅላት፡፡ ስሜቷ ግልፅ ካልሆነልህ ግን በቀጥታ በጣም የፍቅር ሰው እንደሆነችና አንተም እንደወደድካት በመግለፅ ያላትን ስሜት እንድትነግርህ ጠይቅ፡፡ ምላሹ እሷም እንደምታፈቅርህ ከገለፀች ፍለጋህ ተሳክቷል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በቀጥታ ደስ የሚል የፍቅር ሽሚያ ውስጥ የሚያስገባችሁን መንገድ ልትከተሉ ትችላላችሁ፡፡ ለምላሿ ጊዜ የምትፈልግ ከሆነም ጊዜ ስጣት ምላሿ ግን ከአንተ ጋር በፍቅር መቆየት እንደማትፈልግ ወይም ሌላ በፍቅር የምትወደው ጓደኛ ካላትና ለእሱ የምትሰጠውን ፍቅር ለአንተ መስጠት የማትችል ከሆነ በዚሁ የፍቅር ፍለጋህን ልታቆም ይገባል፡፡ ከዚህ በላይ እርግጠና ያልሆንከውን ነገር ይዘህ በመጓዝ ጊዜህን ማባከንም ሆነ ከማትሆንህ ሴት ጋር በመኳተን ጭንቀት ውስጥ በመግባት ህይወትህን ከምታበላሽ በጊዜው መፍትሄ ስጠው፡፡ አንተንም የምትብቅ ለአንተ የታሰበችና የተቀመተች ሌላ ሴት ልትኖር ትችላለችና ይህቺ ሴት እየጠበቀችህ ነውና እሷን ብዙ ማስቆም የለብህም፡፡ የሕይወትህን አቅጣጫ ቀይረውና ሌላ ሙከራ ውስጥ ግባ!

Most Popular

To Top