ዜና

ጓደኞቼ መጥፎ ሽታ ትሸተናለህ ይሉኛል፣ ሽታው ከየት የመጣ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ የማላውቀው ፈተና ገጥሞኛ በፈተናና በስቃይ እገኛለሁ፡፡ ይኸው ከአፌ ይሁን ከአፍንጫዬ ከየትኛው እንደሆነ የማላውቀው ሽታ እንዳለ ጓደኞቼ ይነግሩኛል፡፡ ይህ ሽታ ለእኔ ባይታወቀኝም እነሱን እንደሚያስጨንቃቸውና እንዲርቁኝ እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡ ሆስፒታል ሄጄ ለዶ/ር ይሄ ችግር አለብኝ ብዬ ለማስረዳት ተቸግሬያለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ሄጄ አፌ እየሸተተ ተቸግሬያለሁ ብዬ ስናገር አፍህን ለምን አታፀዳም? ከማለት በቀር መፍትሄው ይሄ ነው ብሎ ሊረዱኝ አልሞከሩም፡፡ ምናልባት ጥርሴ እንደሆነ ብዬ የጥርስ ሐኪም ሳማክር H2O2 የተባለውን መድሃኒት አዘውልኝ ጠዋት ጠዋት አፌን ብታጠብበትም ያመጣልኝ አንዳችም ለውጥ የለም፡፡ እናም ይህ ችግር ትምህርቴን ለማቋረጥ እንድችል እየገፋፋኝ ይገኛል፡፡ ቤተመፅሐፍት ለመጠቀም ወደማልችልበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ የነበረኝ የማስታወስ ችሎታዬ ተሟጦብኝ ከደካማ ተማሪዎች ተርታ ለመሰለፍ ተቃርቤያለሁ፡፡ ተስፋ መቁረጥ እየተሰማኝ አንድ አንዴ ህይወቴንም ለማጥፋት እየገፋፋኝ ነው፡፡ ውድ ወገኖቼ ከዚህ ተስፋ መቁረጥና ጭንቀት ተገላግዬ በደስታ አላማዬን አሳካው ይሆን? እናም፡-
1. የአፍ ሽታ ከሆነ ምልክቶቹን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ብትገልፁልኝ፤
2. የአፍንጫ ከሆነ ምልክቶቹ (እንዴት ማወቅ እንደምችል) ምን አይነት ምርመራ በማድረግ? ከሆነስ ለማስወገድ ልጠቀምበት የሚችልበት ዘዴ መድሃኒትም ካለው ብትገልፁልኝ፡፡
ከበደ183A7159-

የዶ/ር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፡-

ውድ ከበደ፡- ጓደኞችህ ከአንተ መጥፎ ሽታ እንደሚሸታቸው ከገለፁልህ እውነትም ከሰውነትህ (ከአፍህ ወይንም ከአፍንጫህ) መጥፎ ሽታ ይወጣል ማለት ነው፡፡ ሽታው በቀን ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚኖር ነገር ግን ለአንተ ባይሰማህ ሊገርምህ አይገባም፡፡ ምክንያቱም የስሜት ህዋሶቻችን ይበልጥ የሚነቃቁት ከወትሮው የተለየ መረጃ ሲያገኙ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የስሜት ህዋሶቻችን የስሜቱን መጠን ከመለየት ይልቅ ከበፊቱ ያሳየውን ለውጥ መለየት ይቀላቸዋል፡፡ ስለዚህ መጥፎ ሽታው ከአፍህም ይሁን ከአፍንጫህ ለብዙ ጊዜ አብሮህ ያለ ከሆነ ላይሰማህ ይችላል፡፡ መጥፎ ጠረኖችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ተሞክሮ እንደሚያሳየው ግን የችግሩ ሰለባ የሆነው ግለሰብ የእውነት ችግር ኖሮበት ሳይሆን አዕምሮ በፈጠረው አፌ፣ እግሬ ወይንም አፍንጫዬ ይሸታል የሚለው ተጨናቂ ብዙ ነው፡፡ ይህ አዕምሮ የሚፈጥረው ችግር ዋነኛ መለያው የቤተሰብ አባል ወይንም የቅርብ ጓደኛ ስለ ሁኔታው አፍ አውጥተው አለመናገራቸው ነው፡፡ ስለ መጥፎ ጠረኑ ከቤተሰብ አባል ወይንም ከቅርብ ጓደኛ በግልፅ ባልተነገረበት ሁኔታ የሚሰሙ ሮሮዎች ግን በአብዛኛው አዕምሮ የወለዳቸው ናቸውና እንደገና ስለ ጉዳዩ ደግመህ አስብበት፡፡ በእርግጥ ጓደኞችህ ወይንም ሌላ ተመልካች መጥፎ ጠረን እንደሚወጣህ ነግረውህ እንደሆነ አስታውስ፡፡ በግምት ወይንም በመተርጎም ሳይሆን በቃል ተነግሮህ እንደሆነ አስታውስ፡፡ ያ ከሆነ ብቻ የሚከተለውን ምክር መከተል ይጠቅምሃል፡፡
በንግግር ወቅት ወይንም በቅርብ ርቀት የሚመጣ ጠረን ከአፍ ወይንም ከአፍንጫ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥ ከየት እንደመጣ ለማወቅ የሚከተለውን ፈፅም፡፡ በቅድሚያ እጅህን በደንብ ታጥበህ አድርቀው፡፡ ከዛም የመዳፍህን ጀርባ በምላስህ ሁለት ሶስቴ ላሰው፡፡ ምራቁ ከእጅህ ላይ እስኪደርቅ ጠብቅና የመዳፍህን ጀርባ አሽተው፡፡ መጥፎ ጠረኑ ከአፍህ የሚወጣ ከሆነ ምራቅህ ያረፈበት የእጅህ አይበሉባ ክፍል መጥፎ ጠረን ይዞ ታገኘዋለህ፡፡ እንዲሁም መጥፎ የአፍ ጠረን ከአፍንጫህ የሚመጣ ከሆነ መጥፎ ጠረን ያለው ንፍጥ ይበዛል፡፡ ሽታውን እንኳን መለየት ቢያቅትህ መግል የመሰለ ንፍጥ ለረጅም ጊዜ ከአፍንጫህ የሚመጣ መሆኑን አስተውል፡፡
ውድ ጠያቂያችን… የመጥፎ ጠረኑን ምንጭ ብቻ ሳይሆን ምክንያትና መፍትሄ ለማወቅ መፈለግህ አይጠረጠርም፡፡ መጥፎ የአፍ ጠረን በአብዛኛው ከአፍ ንፅህና መጓደል እጅግ አልፎ አልፎ ደግሞ ከከረመ የሳንባ ኢንፌክሽን (Empyema) ሊመጣ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከአፍንጫ የሚወጣ መጥፎ ጠረን ዋነኛ ምክንያቱ የከረመ የሳይንስ ኢንፌክሽን (Chronic Sinusitis) መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ውድ እርምጃህ የአፍህን ንፅህና በመጠበቅ ሊጀምር ይገባዋል፡፡ (ይህም በቀን ሁለቴ በጥርስ ቡሩሽ ሳሙና መፋቅ፣ በወር አንዴ አፍን በH2O2 አፉን መጉመጥመጥና የጥርስ ህመም ሲኖር ወደ ጥርስ ሐኪም መሄድ) ከዚህ ባለፈ ችግርህ የከረመ የሳይንስ ኢንፌክሽን አለመሆኑን ለመረዳት ወደ ሐኪሙ ቀርበህ መታየት ያስፈልጋል፡፡ ጠለቅ ያለ ምርመራ ከፈለግህ ከአንገት በላይ ስፔሺያሊስት ሐኪም ጋር ቀርበህ መታየት ለጥርጣሬህ ወይንም ለችግርህ እልባት ይሰጠዋል፡፡ መልካም ጊዜ፡፡

Most Popular

To Top