ዜና

ኢንፌክሽን

dr araya gmariamአዲስ ዘመን፦ኢንፌክሽን ምንድነው?
ዶክተር አርአያ፦ ኢንፌክሽን ባዕድ የሆኑ አካላት ሰውነታችን ውስጥ ሲገቡ የሚፈጠር ሕመም ነው። ባክቴሪያ፣ፕሮቶዙዋ፣ቫይረስና ፈንገስ የተባሉ በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን ህዋሳት ኢንፌክሽን ሊያስከትሉ ይችላሉ።ኢንፌክሽን ሰውነታችንን የተለያየ ቦታ ሊያጠቃ ይችላል። የሳንባ ኢንፌክሽን በቫይረስና በባክቴሪያ አማካኝነት ሊመጣ ይችላል። የሆድ ውስጥ፣ የኩላሊት፣ የጭንቅላትና ሌሎችም ኢንፌክሽኖች በተለያየ ምክንያት ሊከሰቱ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፦ ሕፃናት ላይ በብዛት የሚከሰቱት ኢንፌክሽኖች የትኞቹ ናቸው?
ዶክተር አርአያ፦ሕፃናት ላይ በብዛት ከሚከሰቱት ኢንፌክሽኖች መካከል የሳንባ ምች (ኒሞንያ) ዋነኛው ነው። ይህ በሽታ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን በመግደል የመጀመሪያው ነው። ከአንገት በላይ ያሉ የመተንፈሻ አካላት በቫይረስ ተጠቅተው ቶሎ ህክምና ሳያገኙ ሲቅር ለሳንባ ምች ሊጋልጡ ይችላሉ።
ከእዚህ በተጨማሪ በባክቴሪያ የሚመጣ የሆድ ኢንፌክሽን ሕፃናትን ያጠቃል። በሕፃናት ላይ ከ80እስከ 90 በመቶ ተቅማጥ የሚያመጣው ሮታ የተባለው ቫይረስ ነው። ሞት ባያስከትሉም የጆሮና የጉሮሮ ኢንፌክሽንም በርካታ ሕፃናትን ያጠቃሉ።
አዲስ ዘመን፦ በሕፃናት ላይ የጭንቅላት ኢንፌክሽን ተከሰተ ሲባል ምን ማለት ነው?
ዶክተር አርአያ፦ ማንኛውም ኢንፌክሽን የሚያመጣ ባዕድ አካል ወደ ሰውነት ሲገባ ከደም ጋር ይቀላቀላል። በደም ዝውውር አማካኝነት ሰውነት ውስጥ የተሰራጨው በሽታ አምጪ ባእድ አካል ሜንጅስ ወደተባለው የአንጎል ሽፋን ያመራል።ይህ ቦታ በኢንፌክሽን ሲጠቃ ሜንጃይትስ ወይም የጭንቅላት ኢንፌክኽን ተከሰተ ይባላል። ሕፃናት ላይ በሳንባ፣ በአንጀት ወይም በሌላ ቦታ ኢንፌክሽን ሲከሰት ሜንጅስ ወደተባለው የአንጎል ሽፋን የመሄድ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሕፃናትን የሚያጠቁት ኢንፌክ ሽኖች በምን አማካይነት የሚከሰቱ ናቸው?
ዶክተር አርአያ፦ኢንፌክሽን አንዳንዴ በምን እንደሚከሰት አይታወቅም ።የሳንባ ምችን የሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች ሰማንያ በመቶ በትንፋሽ ይተላለፋሉ። በንክኪም ወደሕፃናት ኢንፌክሽኖች ሊተላለፉ ይችላሉ። የግልና የአካባቢ ንፅሕናን ካለመጠበቅ ይከሰታል።
አዲስ ዘመን፦ ሕፃናት ህመም ሲያጋጥማቸው እንደ አዋቂ የተሰማቸውን በአግባቡ መግለጽ ስለማይችሉ ኢንፌክሽን ሲያጋጥማቸው እንዴት ማወቅ ይቻላል?
ዶክተር አርአያ፦ የኢንፌክሽን ምልክት እንደ በሽታው ይለያያል።ይሁን እንጂ በብዙ ሕፃናት ላይ ኢንፌክሽን ሲከሰት የሚታዩ ምልክቶች አሉ።ትኩሳት አንዱ ምልክት ነው። ይህ በአዋቂዎች ላይም ይታያል።ሆኖም ግን በሕፃናት ላይ ለየት የሚያደርገው የሰውነታቸው ሙቀት ሊቀንስም ይችላል። ሕፃናት በሜንጃይትስ ሲያዙ እንደሚጥል በሽታ የማንቀጥቀጥ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ማስመለስ፣ ማስቀመጥ፣ራስን መሳት፣አለማልቀስ፣ አለመጥባት፣ንቁ አለመሆን የኢፌክሽን ምልክቶች ናቸው። ቢጫ ዓይነት ቀለም ማምጣትም አንዱ የኢንፌክሽን ምልክት ነው።
በሕፃናት ላይ የሚታዩ የኢንፌክሽን ምልክቶች ትክክለኛ ገላጮች አይደሉም።ሀኪሙ ተጠራጣሪ መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ሕፃኑ ችግሩ ሳይታወቅ ሊሞት ይችላል። ስለዚህ በፍጥነት በአካባቢው ያለው የበሽታ ስርጭት ምን እንደሚመስልና ዕድሜው ለኢንፌክሽን ያለውን ምላሽ ማጣራት አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ሕፃናት ከአዋቂ ይልቅ በኢ ንፌክሽን የሚጠቁት ለምንድን ነው?
ዶክተር አርአያ፦ ኢንፌክሽን ከአዋቂዎች ይልቅ ሕፃናትን ያጠቃል። ምክንያቱም ኢንፌክሽን በሽታ ከመከላከል አቅም (ኢሚዩኒቲ) ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። አንድ ሕፃን ሲወለድ በሽታ የመቋቋም አቅሙ በጣም ዝቅተኛ ነው። በተፈጥሮ ከእናቱ ከሚወስዳቸው አንዳንድ ንጥረ ነገሮች በስተቀር ኢንፌክሽንን ሊቋቋም የሚያስችል የበሽታ መከላከያ የለውም።ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ነው የራሱን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳ ብረው። በእዚህ የተነሳ ኢንፌክሽን በመጀመሪያዎቹ የሕፃንነት ዕድሜ ሲከሰት ገዳይ ይሆናል።ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የመግደል አቅሙ እየቀነሰ ይመጣል።በተለይ ከተወለዱ እስከ ሃያ ስምንት ቀን ድረስ ያሉ ጨቅላ ሕፃናት ላይ ይበረታል።
የአንድና የሦስት ወር ሕፃናት ለአንድ አይነት ኢንፌክሽን ቢጋለጡ ቶሎ የመሞት ዕድሉ ከፍ የሚለው የአንድ ወር ህፃኑ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኢንፌክሽን በሕፃናት ላይ የሚያስከትለው ችግር ምንድነው?
ዶክተር አርአያ፦ የሕፃናትን ሞት ከፍ ከሚያ ደርጉት በሽታዎች መካከል ኢንፌክሽን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። የኢንፌክሽን የመጀመሪያው ጉዳቱ በርካታ ሕፃናትን ለሞት የሚያጋልጥ መሆኑ ነው። የሳንባ ምች ሕፃናትን የሚገድል ኢንፌክሽን ነው። በጭንቅላት ላይ የሚከሰተው የሜንጃይትስ ኢንፌክሽን የሚያጋጥማቸው ከ10 እስከ 20 በመቶ የሆኑ ሕፃናት ሞት ያጋጥማቸዋል። ታክሞ መዳን ቢቻልም ትቶት የሚሄደው ጠባሳ ብዙ ነው። የሚጥል በሽታ፣ ማየትና መስማት አለመቻል፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነትና ግማሽ አካል ያለመታዘዝ ችግር ሊያጋጥም ይችላል። ተቅማጥ የሚያስከትለው ኢንፌክሽን ከሰውነት ፈሳሽን በማውጣት ለሞት ይዳርጋል። ሰውነት ውስጥ የሚፈ ጠረው የምግብ እጥረትም ለሌላ ኢንፌክሽን ያጋልጣል። የሰውነት የመከላከል ብቃትን ያዳከማል። ታክሞ ከዳኑም በኋላ የኩላሊት መድከም ሊከሰት ይችላል።
አዲስ ዘመን፦ ህክምናው ምንድነው?
ዶክተር አርአያ፦ አብዛኞቹ በቫይረስ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች በራሳቸው ጊዜ የሚጠፉ ናቸው።ፀረ ቫይረስ መድሃኒት አይፈልጉም። በባክቴሪያ የሚመጡ ህመሞች ግን በአንቲባዮቲክ(በህመም ማስታገሻ) ይታከማሉ ። ይህ እንደ በሽታው በተለያየ መልክ የሚሰጥ ነው። የሚዋጥ መድኃኒት አለ። በመርፌ መልክ የሚሰጥ አለ።
አዲስ ዘመን፦ ሕፃናት በኢንፌክሽን እንዳይጠቁ ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር አርአያ፦ አብዛኞቹን ኢንፌክሽኖች በክትባት መከላከል ይቻላል። ኩፍኝና ፖሊዮ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ናቸው። እነዚህንና ሌሎች ኢንፌክሽኖችን ሕፃናትን በወቅቱ በማስከተብ መከላከል ይቻላል። የአካባቢን ንፅሕና መጠበቅም ኢንፌክሽንን ለመቆጣጠር ይረዳል።
አዲስ ዘመን፦ ለወላጆች ምን ይመክራሉ?
ዶክተር አርአያ፦ አንድ ሕፃን የተለየ ባህሪ ሲያሳይ ለምሳሌ ይጫወት ከነበረ መጫወት ሲያቆም ፤ትኩሳቱ ሲጨምር ወይም ሲቀንስ ፣ንቁ ካልሆነ (እዚህ ላይ አንድ ሕፃን እንደተወለደ አካባቢ20 ሰዓት ሊተኛ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል)ቢጫ ከሆነ፣ የማይጠባ ፣ የማያለቅስ ፣ በአግባቡ የማይተነፍስ ከሆነ በፍጥነት ባለሙያ ማማከር አለባቸው። ወላጆች የሕፃናትን ሙቀት በቀላሉ በእጃቸው በመያዝ ማወቅ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፦አመሰግናለሁ!

ለግንዛቤ

•ኢንፌክሽን በባክቴሪያ ፣በቫይረስ፣ በፕሮቶዙዋና በፈንገስ ይከሰታል።
•ሰዎችን በተለይ ሕፃናትን በብዛት የሚያጠቁት በባክቴሪያና በቫይረስ የሚመጡ ኢንፌክሽኖች ናቸው።
•ሕፃናትን ከሚያጠቁት የኢንፌክሽን በሽታዎች መካከል የሳንባ ምች ፣ፖሊዮ፣ ሜንጃይትስ፣ ኩፍኝ፣ የሆድ ኢንፌክሽን (ተቅማጥ የሚያስከትሉ)፣የጆሮና የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች ይጠቀሳሉ።
•አንዳንድ በኢንፌክሽን የሚከሰቱ በሽታዎች መላ አካልን ለህመም ሲዳርጉ ሌሎቹ የተወሰነ የሰውነት ክፍልን ብቻ ያውካሉ።
•ትኩሳት፣በተቃራኒው የሙቀት መቀነስ፣ ቢጫ መሆን ፣አለመጥባት ፣አለማልቀስ፣ መጫወት ማቆም በሕፃናት ላይ የሚከሰት ኢንፊክሽን ምልክቶች ናቸው።

Most Popular

To Top